Monday 5 March 2018

እውነት አማኞች

ስለ ታላቁ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ካህን አባ አርሴኒ በተጻፈው አንዱ መጸሃፍ አቭሴንኮቭ የሚባል ባለ ታሪክ አለ። አባ አርሴንይ ለሁለተኛ ጊዜ ጉላግ የሚባለው የሶቪዬት የሞት እስርቤት ገብተው እያለ የመንግስት ባለስልጣንና ዳኛ የነበረው የኮምዩኒስት ፓርቲ አባል አቭሰንኮቭ ታስሮ ወደሳቸው እሰር ቤት ይገባል። እንዴት እንደ አቭሴንኮቭ አይነቱ ከፍተኛ ባለ ስልጣን ታሰራ። ወቅቱ እንደ የኢትዮጵያ ቀይ ሽብር ነበር። የሰው ስልጣን ወይም ስራ ለመቀማት፤ ሰው በመጠቆም ሹመት ለማግኘት፤ የሚጠሉትን ሰው ለመጉዳት፤ ጥቅም ለማግኘት ወዘተ ምክንያቶች ፖለቲከኞችም ብዙሃንም እርሰ በርስ እየተጠቋቆሙ እስር ቤቶቹንና መቃብሮቹን እየሞሉ ነበር። በዚህ ሂደት በርካታ ባለ ስልጣኖችም ታስረዋል ተገድለዋልም። አቭሴንኮቭ አንዱ ከታሰሩት ነበር

አቭሴንኮቭ ሶቪየቶች «እውነት አማኝ» ኮምዩኒስት ከሚሏቸው አንዱ ነበር። ይህ ማለት በኮምዩኒስም ርዕዮተ ዓለም፤ በፓርቲውና በአስተዳደሩ በእውነት ያምን ነበር። «ባለጥቅም» ከሚባሉት ለስልጣ፤ ለገንዘብ፤ ለሹመት፤ ለጥቅም፤ ሰው በማሰርና በማስጨረስ ብሶቱን ለመወጣት ወዘተ አልነበረም የኮምዩኒስት ፓርቲ አባልና ባለ ስልጣን የሆነው። በእውነት የኮምዩኒዝምን መሰረተ ሐሳቦች ያምን ነበር። ለዚ ለሚያምንበት ርዕዮተ ዓለም ለማሳሰር ለመፍረድና በሞት ፍርድ ለመፍረድ ዝግጁ ነበር።

ግን እንደ ማንኛውም ድርጅት ወይም ፖለቲካ ፓርቲ የኮምዩኒስት ፓርቲም በርካታ «እውነት አማኝ» ያልሆኑ አባላት በበረው። እነዚህ ቅድም እንደጠቀስኩት ለስልጣን፤ ለገንዘብ፤ ብሶት ለመወጣት፤ ጥቅም ለማግኘት ወዘተ ፓርቲ ውስጥ የገቡ ናቸው። አንዱ እንደዚህ አይነቱ የአቭሴንኮቭ የከፍተኛ ዳኛ ስልጣንን ለመቀማት ብሎ ቀስ ብሎ ሴራ ፈጥሮ አቭሴንኮቭን ከስሶ ወደ ጉላግ የሞት እሰርቤት እንዲላክ አደረገ።

አቭሴንኮቭ እስር ቤት እንደገበ መታሰሩን እንደ የአስተዳደር ስህተት ነበር የቆጠረው። በኮምዩኒዝምም በመንግስቱና አስተዳዳሪዎቹና መዋቅሮ እምነቱ እንዳለ ሆኖ በስህተት ነው የታሰርኩትና ከትንሽ ጊዜ በኋላ ስህተቱ ተደርሶበት እፋታለው ብሎ ይጠብቅ ነበር። በእውነት አማኞች ዘንድ ይህ የተለመደ አስተሳሰብ ነበር። የእምነታቸው ጥንካሬ የፓርቲውንና የመንግስቱን መሰረታው ሐሳቦች በጥያቄ ውስት ማድረግ እንዳይችሉ ያረጋቸው ነበር።

ግን አቭሴንኮቭ በእስር ቤቱ በቆየ ቁጥር መቀየር ጀመረ። እንደ አባ አርሴኒ አይነቱን በጸረ አብዮትነት የተሳሩትን ባልደረቦቹን ሲመለከት፤ ስነ መግባራቸው፤ እምነታቸው፤ ትህትናቸው፤ ፍቅራቸውን ሲመለከት ንፁሃን እንደሆኑ ቀስ በቀስ መረዳት ጀመረ። ከእስር ቤት አስተዳዳሪዎችና አዛጆቻቸው የሚመነጨው ክፋትን ሲአይ ደግሞ ያምንበት የነበረውን የፖለቲካ መዋቅሩን መጠራጠር ጀመረ። አቭሴንኮቭ ቀስ በቀስ የመንግስቱንና ርዕዮተ ዓለሙን ክፋት እየተረዳ ሄደ፤ ወደ አባ አርሴኒ አይነቱን እያየ ወደ ክርስትና መለወጥ ጀመረ። መጨረሻ ላይ የአባ አርሴኒ ንሰሀ ልጅ ሆኖ ነበር እድለኛ ሆኖ ከእስር ቤት ሳይሞት የወጣው።

ቅድም እንደጠቀስኩት ማንኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ወስጥ እውህነት አማኞችና ባለጥቅሞች አሉ። ሁለቱም አይነቶች አሉ። ብዙዎቻችን እውነት አማኞችን እናከብራለን ባለጥቅሞችንን እንንቃለን። ግን እንደዚህ መሆን አለበትን? ማን ነው በርካታ ጉዳት ሊአይደርስ የሚችለው፤ እውነት አማኙ ወይም ባለ ጥቅሙ? ማን ነው ይበልጥ ክፉ መሆን የሚችለው?

አቭሴንኮቭ ረስቷቸው ነበር እንጂ እሱ ነበር አባ አርሴኒን ፈርዶባቸው ወደ ሞት እስር ቤት የላካቸው። የኮምዩኒዝምና የሶቪዬት ህዝብ ጠላት ናቸው ብሎ። ሌሎችም በርካታ ሰዎችን ወደ እስር ቤትና ሞት ሲልክ ለሚያመልከው ርዕዮተ ዓለም ስለሆነ ሰው መሆናቸው ረስቶ ልቡን ደንድኖ ድርጊቱን በቀላሉ አደረገው። እውነት አማኞች እጅግ አደገኛና ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ። የሚያምኑበት አካዬድ መጥፎ ከሆነ ይህን መጥፎነት በሙሉ እምነትና አቅማቸው ስለሚያራምዱ በርካታ ጉዳት ይፈጽማሉ። እውነት አማኝ በጥሩና ትክክለኛ ነገር ካመነ በጣም ጥሩ ውጤት ይኖረዋል። በመጥፎ ነገር ካመነ ደግሞ መጣም ከባድ ጉዳት ያደርሳል።

ባለጥቅሙ ግን ልቡ በሙሉ ስለማያምንበት የሚፈጽመው ጉዳት አናሳ ሊሆን ይችላል። ከጥሩም ከመጥፎም ወገን ቢሰለፍ ውጤቱ መካከለኛ ነው የሚሆነው። ክፉ ስርዓት ውስጥ ከተሳተፈ የሚያመጣው ጉዳት እንደ እውነት አማኙ ላይሆን ይችላል። ጥሩ ስርዓት ውስጥም ቢሳተፍ ወጤቱ እንደ እውነት አማኙ ያህል አይሆንም።

ስለዚህ እውነት አማኞችን ከባለጥቅሞች ይበልት ልናከበራቸው አይገባም። የአብዛኛው ጸንፈኛ የፖለቲካ ንቅናቄዎች መሰረት ጠንካራ የእውነት አማኝ ቡድን እንደሆነ መርሳት የለብንም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ ከተመለከትን የግራ ርዕዮተ ዓለም ትከታይ የሆነው የተማሪ ንቅናቄ የደረሰበት ደረጃና ያደረሰው ጉዳት አለ እውነት አማኞች አይሆንም ነበር። ላይ ያሉት መሪዎች መካከል በርካታ ባለጥቅሞች ቢኖሩም አለ ጠንካራ የእውነት አማኝ አምድ የትም አይደርሱም ነበር። እነ ህወሓትና ሻብያም የእውነት ዓማኝ አምዳቸው ነው እዚህ ያደረሳቸው አንዳይታደሱም የሚከለክላቸው።

ለኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳታፊዎች ይህ ታላቅ ትምህርት ሊሆነን ይገባል። «አምኖበት ነው ያእደረገው» «ለአቋሙ የቆመ ነው» «ፕሪንሲፕለድ ነው» «ለአገር ብሎ ነው ያደረገው» አይነቱን አባባሎቻችንን መተው አለበን። አንድ ሰው የሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም ክፋት የሚጎትት ከሆነ እውነት ዓማኝ መሆኑ «ፕሪንሲፕልድ» መሆኑ ምን አይጠቅምም። ጭራሽ ጉዳት ነው። በደምብ ስለሚያምንበት ይበልጥ ጉዳት ያደርሳልና። ዋናው አላማችን በተሳሳተ ርዕዮተ ዓለም ወይም አቋም አለማመን። በተቻለ ቁጥር ማንኛውም ርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ አመለካከት ከሰው በላይ አለማረግ። ዋናው ነገር ሰው ነው። ለሰው የሚያስፈልገው ፍቅርና ፍትህ ነው። ሌላው በሙሉ እነዚህን ማግኛ ዘዴ ነው። የምናምንበት ርዕዮተ ዓለም ጭራሽ ጥላቻና ጉዳት እያደረሰ ካየን የተሳሳተ መሆኑን ቶሎ ተረድተን መተው መቻል አለብን። ጣዖታችን ሊሆን አይገባም። ከኢግዚአብሔር በቀር ለምንም የእውነት አማኞች መሆን የለብንም።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!