Monday 26 March 2018

ቀደም ተከተል

በ«ተቃዋሚዎች» መካከል ስለ አማራ ማንነት አይነቱ ክርር ያለ ጭቅጭቅ ሲነሳ «መጀመሪያ የሁላችንም ጠላት የሆነውን ህወሓትን ከስልጣን መፈንቀል ላይ ተባብረን እናተኩር ፤ ከዛ በኋላ ስለ ሌሎች ጉዳዮች መነጋገር ይቻላል» ይባላል።  ለ27 ዓመት በተደጋጋሚ የሰማነው አሁንም የምንሰማው አባባል ነው።

አዎ ግባችን ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ ከሆነ ከማንም ጋር ተባብረን ሌሎች ጉዳዮችንን በሙሉ ዘርግፈን ግባችን ላይ ማተኮር ነው ያለብን። ነገር ግን ይህን ማድረግ አልተቻለም። ለ27 ረዥም ዓመታት አልተቻለም! ተስማምተን ለአላማችን ብለን ተማምነንና ተባብረን አንድ ሆነን መስራት አልቻልንም።

ለምን? ለምን ግባችንን ለመምታት ግድ የሆነውን አንድነት መመስረት አልቻልንም? ያልቻልንበት ምክንያት እኛ «ተቃዋሚዎች» በርካታ የማንስማማባቸው የአገራችን የፖለቲካ ጉዳዮች ስላሉ ነው። በነዚህ ጉዳዮች ስለማንስማማ ተማምነን አብረን መስራት አልቻልንም።

ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት ቁጭ ብለን መወያየት፣ ጉዳዮቹን ማብሰልሰል፣ መከራከር፤ መስማማት አለብን። ይህን የውይይት ስራችንን እስካሁን በጭራሽ አልሰራንም ማለት ይቻላል። እስካሁን ጊዜአችንን አቅማችንን 95% በኢህአዴግ ማልቀስ 5% በራሳችንን ማጎልበት ነው ያዋልነው! አንድ ላይ መስራት የምንችለው በኢትዮጵያ ያለንን ራዕይ ዙርያ በቂ ውይይታዊ ስራ ካደረግን በኋላ ነው።

ስለዚህ ቀደም ተከተሉ እንደዚህ መሆን አለበት፤ 1ኛ) እርስ በርስ ያለንን ጉዳዮች ተወያይተን ጨምቀን ወደ የምንተመመንበት  የምንስማማበት መድረስ። ይህ ስራ ዓመታት ሊፈጅ ይችላል። 2ኛ) ከዚያ በኋላ የመሰረትነውን መተማመን፣ ስምምነትና አንድነት ተጠቅመን ህወሓትን መፎካከር።

ለማጠቃለል ትኩረታችን ህውሓትን ከስልጣን ማውረድ ከሆነ በመጀመሪያ በመካከላችን አንድነት መፍጠር አለብን። አንድነት ለመፍጠር እርስ በርስ በሁሉም መልኩ እንዳንተማመን፤ እንዳንስማማ እና አንድነት እንዳንፈጥር የሚያደርጉንን ጉዳዮች በደንብ መወያየት አለብን። ከዚያም የገነባነውን አንድነት በመጠቀም ህወሓትን ለማሸነፍ እንችላለን።

ስለዚህ ስለ አማራ ማንነት፤ የጎሳ አስተዳደር፤ የትግል ስልት፤ እና ሌሎች በርካታ የማያስማሙን ወይም ማሻሻል የሚኖሩብን ጉዳዮችን መወያየት ህወሓትን ለማሸነፍ የግድ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ቅድመ ሁኔታ ነው።

እዚህ ላይ ለመጨመር ያህል በኔ እይታ ህወሓትን ከስልጣን ማስወገድ አንደኛ ላማችን ሊሆን አይገባም። አላማችን ሰላም፤ ፍትሕ፤ ፍቅር፤ መልካም አስተዳደር ማምጣት ነው። ሀውሓትንም ማስወገድ የምንፈልገው የነዚህ ተቃራኒ ስለሆነ ነው። ግን ህወሓትን ከስልጣን አባረን የሱን ቢጤ የሆነ መንግስት አንፈልግም። ከላይ የዘረዘርኩት አካሄድ ግን እንደዚህ እንዳይሆን የሚከላከል ነው! ስለ አገራችን ያለንን ራዕይ ላይ ቀድሞ በደምብ ተወያይተን ከተስማማን ከተማመንን አምባገነን ከመካከላችን አምባገነን ሊፈጠር አይችልም አምባገነን የአለመግባባት የአለመስማማት ውጤት ስለሆነ። ስለዚህ ካሁን ወድያ ይህ ዋና ስራችን ላይ እናቶኩር።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!