Wednesday 5 October 2016

ፖለቲካ ሃይማኖት አይደለም!

2009/1/24 .. (2016/10/4)

(pdf)

ዛሬም ጠንካራ፤ ህዝብን የሚወክል፤ ኢህአዴግን በመጠኑም ቢሆን ሊጋፈጥ የሚችል የተቃዋሚ ድርጅት በኢትዮጵያ የለም። (ደህና የሚባለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስም በምንም ሚዛን እነዚህን መስፈርቶች አያሟላም።) ይህ እውነታ ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ የዛሬው የህዝብ እንቅስቃሴ ከቀጠለና ከጨመረ አለመሪነትና ድርጅት እንዴት ይሆናል ብለን እንሰጋለን።

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ለ25 ዓመት ደህና ተቃዋሚ ድርጅት ኖሮ አያውቅም። የነበሩትም ያሉትም ደካማ፤ በቀላሉ የሚፈሩና የሚበታተኑ፤ እርስ በርስ ተጣልተው እራሳቸውን ከጥቅም ውጭ የሚያደርጉ ወዘተ ናቸው።

የዚህ ሁኔታ ያልሆነበትን ምክንያት ተጠንቅቀን እናውቃቸዋልን። ኢህአዴግ ጠንካራ ስለሆነ አይደለም። ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ ጥቂት ህዝብ ነው የሚወክለው እያልን በዛው ትንፋሻችን ጠንካራ ነው ማለት አንችልም!! ኢህአዴግ በኃይሉ ሳይሆን በፈቃዳችን እንደሆነ የሚገዛው እናውቃለን፤ እራሳችንን አናታልል።

ታድያ ለምንድነው ተቃዋሚው ለመደራጀትም የሚያቅተው። እንደምናቀው አንዱ ዋና ችግር የተቃዋሚ ፖለቲከኖችም ህብረተሰብም የአለመስማማት፤ እርስ በርስ መጣላት፤ እሩቅ ማሰብ አለመቻል፤ ወዘተ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ተጽፏል። ሆኖም ከዚህ ጽሁፍ አንድ ሌላ ተቃዋሚን የሚያደክመው ምክንያት ላቀርብ እወዳለሁ፤ ይህ ፖለቲካን እንደ ሃይማኖት ማየትና የሚከተለው ግትርነትና አለመቻቻል።

ሃይማኖት በአንድ እውነት የተመሰረተና የማይቀየር ነው። ለምሳሌ እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያንነቴ ክርስቶስ ሞተና በሶስተኛው ቀን ተነሳ ብዬ አምናለው ከዚህ እምነትም ዝንፍ አልልም፤ ይህ ፍፁም እውነት ነውና።

ግን ይህንን ዝንፍ አለማለትን ወደ ፖለቲካ ወይም ሌላ የህይወት ዘርፍ ማምጣት የለብኝም። ቅንጅት ፓርላማ ይግባ አይግባ ፍፁም እውነት ያለው የሃይማኖት ጉዳይ አልነበረም፤ ከሁለቱም አቋሞች ጥሩ የሆኑ የሚያስኬዱ ምክንያቶች ነበሩ። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ጎሳን ያካትት አያካትት፤ ይህም የድርድር ጉዳይ ነውንጂ እውነትና ውሸት የለበትም። ወዘተ። በፖለቲካ ወይም በስራ ወይም በቤተሰብ ኑሮ መደራደር፤ የሌላውን አስተያየት መረዳት፤ ለሌላው መቆርቆር፤ ላለመስማማት መስማማት፤ ወዘተ አስፈላጊ ነው።

ለምሳሌ ስንቶቻችን ነን የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞቻችንን ቀይረን የማናውቀው? አንዳንዶቻችን የኃይለ ስላሴን መንግስት በግዜው እንደግፍ ነብር ዘሬ ግን ዴሞክራሲአዊ አለመሆኑን አንወድም እንላለን። ስንቶቻችን በኮምዩኒዝም በኢህአፓ ወዘተ እናምን ነበር ዛሬ ግን ተሳስተን ነበር እንላለን። ስንት የደርግ ደጋፊ የነበሩና አሁን ንስሃ የገቡ አሉ። እርግት ኢህአዴግንም በአንድ ወቅት የደገፉ አሉ!

ታድያ ሃሳባችንን ሲያስፈልግ የምንቀይር ከሆነ ለምንድነው ከኛ ፖለቲካዊ ሃሳብ ጋር የማይስማማ ባልደረባ ሲያጋጥመን ከሱ ጋር ጦርነት የምንገባውም የጋራ ፖለቲካ ድርጅታችንንም የምናፈርሰው?! ይህ የሚሆነው ፖለቲካን እንደ እምነት ምንም ድርድር የማይደረግበት ነው ብለን ስለምንቆጥር ነው።

በፖለቲካ ደረጃ መስማማት፤ አለመከፋፈል፤ አንድ መሆን ከፈለግን የሃሳብ ልዩነቶችን በሚገባው በትህትና መቀበልና ማስተናገድ አለብን። የግትርነትና አጉል እረግጠኝነት መንፈሳችንን ማስወገድ አለብን። እንደዚህ ማድረግ ስንችል፤ በተለይ የፖለቲካ ትህትናችንን ማዳበር ስንችል ነው የተቃዋሚ ድርጅቶቻችንን በቂ አቅም እንዲኖራቸው ማድረግ የምንችለው።

ትህትናና ግትር አለመሆን፤ እነዚህን ብቻ እናስታውስ።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!